ቅዱስ ያሬድ በክዋኔ ጥበብ ፍልስፍና

admin
Saint Yared
09 Mar, 2023

ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያ በማናቸውም ምድራዊና ሰማያዊ እውቀትና ጥበብ ረሀብ ዐይኖቿ በቅልውጥ ሩቅ እንዳያንጋጥጡ የደለበ ትሩፋትና በረከት ሰጥቷታል፡፡ ጥበብ ምድራዊ ጥበብ ሰማያዊን ናኝቷታል፡፡ ይሁን እንጂ የምርጫ ጉዳይ ይሁን አለማወቅ ኢትዮጵያ ታች ወርዳ ከጨቅላ የአውሮፓና ምዕራባዊ አገራት የእውቀትና የትምህርት ፈሊጥ ማምጣቷ አልቀረም፡፡ ይህም ብቻ ሳይበቃ ደግሞ የራሷን እንደሌለ በመቁጠር ሊቃውንቶቿን የአውሮፓ እውቀት፣ ጥበብና ፍልስፍና ቅኝ ተገዢ የምታደርግበትን የትምሕርት ሥርዓት ተቀብላና ቀርጻ ራሷን አንቆ በመግደል የማጥፋት ያህል አበክራ የሰራች አገር ለመሆኗ ገሀድ ነው።

እውቀት ድንበርና ወንዝ ሳይገድበው የሚቀባበሉትና የሚጋሩት ቀመር ሲሆን የተመጣጠነ የእውቀት ሽግግርና አዕምሯዊ ብልጽግና ነው። ከአንድ ወገን ብቻ የሚፈስ ከሆነ ግን የራስን ማንነትና ፍልስፍና የሚደፈጥጥ፤ አገር በቀል እና አገር አቅኚ እውቀትን ደራሽ ጎርፍ ሆኖ የሚያጥለቀልቅና የሚቀብር ደለል ይሆናል፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ከመቶ ዓመታት በላይ እየዳከረች ስትድፈነፈን የቆየችው ኢትዮጵያ ካጣችውና ከተጎዳባት የእውቀት ዘርፍ አንዱና ዋናው የክዋኔ ጥበብና ስነ ውበት ፍልስፍና እውቀቷ ነው፡፡ በዚህም በክዋኔ ጥበብ እና ስነ ውበት ፍልስፍናዋ ቀጭጫ የራሷን እውነት መኖር የተሳናት፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው የጥበብ ሥራዎች ለመስራት በመቸገር ናክላለች። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ኢትዮጵያ ዛሬ የሌሎችን ዕውቀት መድህን አድርጋ ከድህነት ለመውጣት አለመቻሏና ከውድድሩ ዐውድ አሸንፋ ባለመውጣቷ እንደሚገለጽ ብዙ አዋቂዎችና ተንታኞች ይተቻሉ    

እርግጥም እስከዛሬ የቀጠለውን የአርኪዎሎጂ ምርምሮች ተጎዳኝቶ፣ የአምፊ ትያትር ቅርጽ ያላቸውን ትርዒት ማሳያ ዐውዶች፣ ረቀቅ ያለ የእደ ጥበብ አቅም ጎልቶ የወጣባቸውን ቅርሳ ቅርሶች እና የወግ መገልገያ ቁሶቻችንን፣ የድንጋይ ላይ ጽሑፎችን፣ የአብያተ እምነት የአምልኮ ስርዓት አፈጻጸም እና ድርሳናቱን በማጥናት የትያትራችንን አጀማመርና ጥንተ ተፈጥሮ በምርምር ማግኘት ይቻላል፡፡ ለዚህ አብነት ይሆን ዘንድ በቅዱስ ያሬድ ዙሪያ ተጠርዘው የተቀመጡ የዜማ ድርሰት መጻሕፍትን እና የዜማዎቹን የፍልስፍና መሰረት ማጥናት ግድ ይላል፡፡

ቀደም ሲል በርካታ ምሁራን ቅዱስ ያሬድ ለዐለም ዜማ መሠረት መሆኑንና የግዕዝ ቅኔና አማርኛ ሥነ ግጥም መሠረት መሆኑን አጥንተዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ሊቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ከዚያም በላይ የስነ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ የማህበራዊ ሕይወት አደረጃጀት፣ የስነ ምግባርና ስነ ልቡና እውቀቶችና ፍልስፍና ያላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ጥልቅ የክዋኔ ጥበብ እና የስነ ውበት ፍልስፍና ቀመር ይታይባቸዋል

የቅዱስ ያሬድን የክዋኔ ጥበብና የስነ ውበት ፍልስፍና ከየትኛውም የውጪ አገር ንድፈ ሀሳቦች ጋር በማነጻጸር ያልተገባ ፍረጃ መስጠት መልካም ባይሆንም ከዐለም ከሚጋራቸው የክዋኔና የትያር ጥበብ ባህርያት መነጠልም ደግሞ አስፈላጊ አይደለም። ስለዚህ የቅዱስ ያሬድን የክዋኔ ጥበብና የስነውበት ፍልስፍና በሌሎች ቀመር እየነጸሩ መፈተት ሳይሆን የራሱን አስተምህሮ የክዋኔ ጥበብንና ስነ ውበት ፍልስፍና እያራቀቀ እውቀትን የተጠበበትን ዘይቤ መመርመርና የፍልስፍና ፈለጎቹን ጥልቀት ማጥናት ከምሁራን ይጠበቃል።