ውድ የቅዱስ ያሬድ ቤተሰቦች ሰላም ለእናንት ይሁን!
ኢትዮጵያ ያአሬዳዊ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ሥነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት የቅዱስ ያሬድን አስተምህሮ የተግባራዊ ልምምዳችን አካል ለማድረግ ለሚያደርገው ጥርጊያውን የሚያቀኑ ሁለት ዐበይት የፕሮጅክት ሀሳቦችን መተግበር ይጀምራል።
- የወጣቶችና ጎልማሶች አቅም ግንባታ ፕሮግራም
ከ6ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቅዱስ ያሬድ የተመሰረቱትን ጨምሮ በርካታ የአብነት ትምሕርት ቤቶች ተመሥርተዋል። እነዚህ ትምሕርት ቤቶች ስማቸው በአገራችን በገናናነት የሚነሱ ሊቃውንትን ማፍራት ችሏል። ዘመናዊ የምንለው የምዕራቡ ዓለም የትምሕርት ሥርዓት እስከተስፋፋበት ቅርብ ግዜ ድረስ ከእነዚህ የአብነት ትምሕርት ቤቶች የሚወጡ ሊቃውንት ፍትሐ ነገሥትን በመተርጎምና የሕግ ሥርዓትን በማስፈን፤ የመንግሥት አስተዳደርን በማዋቀርና በመምራት፤ ማህበራዊ ሕይወትን በእውቀት በማደላደልና ኢትዮጵያ የተባለች ታላቅ አገር በማነጽ፤ ስልጡን ማህበረሰብ በመፍጠር ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
የቅዱስ ያሬድ አምስቱ ጸዋትወ ዜማ ድርሰቶች ለመንፈሳዊ አገልግሎት ቤተ ክርስቲያን ከምትጠቀምበትም በላይ ለአገር ግንባታ የሚያበረክተው አገር አቅኚ እውቀት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። በኢትዮጵያ ምድር የበቀሉ እኒህ አገር ያቀኑ የቅዱስ ያሬድ እውቀቶች ከስድስተኛው እስከ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የዘለቀ ወርቃማ ዘመን የፈጠር ነው። ይሁን እንጂ እንደ አገር እኒህን የቅዱስ ያሬድ አገር አቅኚ እውቀቶች በተገቢው ደረጃ አልተጠቀምንባቸውም። ይልቁንም እኒህን ኢትዮጵያዊ ጠባይ ያላቸው አገር ያቀኑ እውቀቶች መማርና ማጥናት እንደኋላ ቀርነት ሲቆጠር ቆይቷል።
ምንም እንኳ “ዘመናዊ” ለሚባለው የምዕራቡ ዓለም የተምሕርት ሥርዓት ካለን ፍቅር፣ ክብርና ከምንሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የተነሳ እኒህን በኢትዮጵያ ምድር የበቀሉ አገር አቅኚ እውቀቶች የማጣጣል ከንቱ አባዜ ቢስፋፋና በአብነት ትምሕርት ቤት ጠንቅቀው ያለፉ ሊቃውንትን እንደአላዋቂ መግፋት ቢኖርም የቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚሰጠው ክብርና ዋጋ አንጻር ዛሬም ድረስ አገር አቅኚ ይዘቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ይልቁንም ኢትዮጵያ እንደወረደ የተቀበለችው የምዕራቡ ዓለም ሥርዓተ ትምሕርት በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አውድ ውስጥ ያበረከተው ጉልህ አስተዋጽዖ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊ ጠባይ የሚታይባቸውን እውቀቶች አጽንቶ ሥልጡን ማህበረሰብ ለመፍጠርና ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ለመመልስ የሚታይበትን ውሱንነት ለመቅረፍ የቅዱስ ያሬድን አስተምህሮ ችሮታ ዘመኑ ሊጠይቅ ግድ ብሎታል።
በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ያሬዳዊ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ሥነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት የቅዱስ ያሬድን አስተምህሮ በማስፋፋትና በማበልጸግ አገራችን ለተያያዘችው ሁለንተናዊ የለውጥ ሂደት የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
የአብነት ትምሕርት ቤት ተማሪዎች ከ5-7 የሕጻንነት ዕድሜያቸው ፊደል በመቁጠር ይጀምራሉ። ከዚያም የፊደላትን ዘር በሚገባ ከለዩ በኋላ ንባብ ተምረው ወደቃል ትምሕርት ይሸጋገራሉ። ከቃል ትምሕርት ወደዜማ በየደረጃው አድገው እስከ መጻህፍት ትርጓሜ ድረስ የሚዘልቅ ከፍተኛ ጥረትንና ትጋትን የሚጠይቅ ማዕርግ ይደርሳሉ።
በአገራችን በሚታየው ነባራዊ ሁኔታ እኒህ የልጅነትና የወጣትነት ዕድሜያቸውን በዚህ የትምሕርት ሥርዓት ያሳለፉ ወጣቶችና ጎልማሶች በ”ዘመናዊው” የትምሕርት ሥርዓት እስካላለፉ ድረስ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የመቀጠር ዕድል ካላገኙ በስተቀር ከጉልበት ሥራ በስተቀር እንደተማረ ሰው በኢትዮጵያ ምድር የመንግሥት ሥራ የሚያገኙበት ዕድል የለም። በዚህ ምክንያት እነዚህ ዜጎች አብዛኛውን የዕድሜ ዘመናቸውን ያሳለፉበት ትምሕርት ውኃ በልቶት እንዳለተማረ ሰው ከሥራ ተገልለው ከእጅ ወደአፍ በሆነ አድካሚ የጉልበት ሥራ በጉስቁልናና ድህነት ይማቅቃሉ።
ከአብነት ትምሕርት ቤት የሚቀሰሙ እውቀቶች ዛሬ በዚህ ደረጃ የተቀበልናትን ኢትዮጵያ የስልጣኔ እምብርት አድርጓታል፣ ዛሬም ድረስ በተለያዩ አሉታዊ ግብር እየተቀጠቀጠ ሊፈርስ ያልቻለ ጠንካራ እሴቶች፣ ወግ ልማድና ባህል ፈጥሯል፤ ለሰላምና ለአንድነት የማይፈታ ጠንካራ ማህበራዊ መደላድል ፈጥሯል፤ በጽኑዕ መሠረት ላይ የቆመ በአገሩ አንድነትና ልዕልና የማይደራደር ዜጋ አፍርቷል፤ ከስድስተኛው እስከ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የዘለቀ የኢትዮጵያን ወርቃማ ዘመን ናኝቷል። ስለዚህ ድርጅታችን ይህን አገር ያቀና እውቀትና የእውቀቱ ባለቤት ሊቃውንትን በቁጭትና ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ ልትጠቀምባቸው፤ ከወደቁበትም ልታነሳቸው ግድ ነው።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በርካታ ቁጥር ያላቸው የአብነት ትምሕርት ምሁራንና ሊቃውንት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ገዳማትና አድባራት ዙሪያ ከተቋቋሙ የአብነት ትምሕርት ቤቶች አገር ሊያቀና የሚችል ውድ እውቀት ቀስመው የዕለት እንጀራ ለማግኘት ሲሉ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች በአድካሚና እንደልፋቱ ብዙ ገቢ በማያገኙበት የጉልበት ሥራና በኮንስትራክሽን ሙያ ተሰማርተው ይገኛሉ።
ድርጅታችን አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የሚገኑ እንዚህን ወታቶች በማሰባሰብ ከተማሩት ትምሕርት ጋር ተያያዥነት ባላቸው የሙያ ዘርፍ አሰልጥኖ ለረጅም ግዜ በቀሰሙት እውቀት ደግሞ ራሳቸውንም ጠቅመው አገርንና ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉበትን ስልት በመንደፍ ሊቃውንቱን እንደዜጋ ከብክነት ለማትረፍ እና እውቀታቸውንም እንደአገር ሀብት ለመጠቀም የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
- ጥበብን በጥበብ!
እንደ አገር ቅዱስ ያሬድን የምናውቀው ይመስለናል እንጂ አናውቀውም። ለዚህ እንደዋቢ የሚጠቀሰው ቅዱስ ያሬድን እንደአገር በሚገባ አውቀንው ቢሆንማ ኖሮ አገር ያቀና አስተምህሮውን ተጠቅመን የቀደመ ሥልጣኔያችንን ዳግም እንኖረው አልነበረምን? የሚለውን ተጠየቅ ማስነሳቱ ነው።
እርግጥ ነው ቅዱስ ያሬድን በተገቢው ደረጃ አላወቅነውም፤ ይህ ማለት ደግሞ ከእንግዲህም ልናውቀው አንችልም ማለት አይደለም። ይልቁንም አብዝተን በመሥራት የባከነውን ግዜ ለማካካስ መፍተን ይኖርብናል።
አብዛኛውን ዜጋና የማህበረሰብ ክፍል በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ እውቀትንም ሆነ አዋቂዎችን ለማስዋወቅና ለመተዋወቅ ቀላሉ መንገድ የኪነ ጥበብና የሚዲያ አማራጮችን መጠቀም ነው።
በቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ሥራዎቹ ዙሪያ እስካሁን ኝዛቤ ከመፍጠርም ባሻገር ሥራዎቹን በሚገባ ለመረዳት የሚያስችሉ በርካታ መጻሕፍትና ድርሳናት ልናነብ በምንችለው ቋንቋና ቀለል ያለ አዝገጃጀት በገበያ ላይ ቢውሉም ሊቃውንቱና ጥቂት ስለ ቅዱስ ያሬድ ለማወቅ ፍላጎት ያላቸው ምሁራን ካልሆኑ በስተቀር ከዳር እስከዳር ተነባቢ ሆነው አዎንታዊ ቁጭት የሚፈጥሩ አልሆኑም። ስለዚህ የቅዱስ ያሬድንም ሕይወትና ሥራዎቹን በሚገባ ለመተዋወቅና ለማስተዋወቅ ሚዲያና ኪነ ጥብበን መጠቀም ተገቢ አማራጭ የማይገኝለት መፍትሔ ነው።
በዚህ መሠረት ከየሙያ ዘርፉ በአገር ውስጥ አሉ የተባሉ ታላላቅ የኪነ ጥበብ ሰዎች የሚሳተፉበት ታላቅ የኪነ ጥበብ ሥራ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ምስጢራዊነቱን ለመጠበቅ ሲባል ከዚህ በላይ ምንም ማለት አስፈላጊ ባይሆንም ዝግጅቱ ሲጀመር ጀምሮ የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ አባላት ሂደቱን የሚከታተሉበት ስልት ተዘጋጅቶ የዝግጅቱ አካል እንዲሆኑ ይታሰባል።
አሁን ባለበት ደረጃ ስለጥበብ ሥራው ማለት የሚቻለው በዐለም አቀፍ ታላላቅ መድረኮች የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት የቅዱስ ያሬድን ሕይወትና ሥራዎቹን ከአጥናፍ አጥናፍ ለመናኘትና በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል ፕሮዳክስን እንደሚሆን ይጠበቃል።
ውድ የቅዱስ ያሬድ ቤተሰቦች በዚህ ዙሪያ ታላላቅ ሥራዎችን ለመሥራትና የምንመኘውን የኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመን እውን ለማድረግ ከፊታችን በርካታ ሥራዎችን እንደቤተሰብ መሥራት ይጠበቅብናል።ስለዚህ እያንዳንዱ የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ አባል የሆነ ሁሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ቤተሰቡን ተቀላቅለው እንድንበዛና በዚያው ልክ የሀሳብ ጉልበት ፈጥረን የምንደመጥበትን ዕድል መፍጠር አለብን። አገር ያቀኑ እውቀቶቻችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም የምንችለውን ሁሉ መሥራት ይኖርብናል። ይህን ውጥን እውን ለማድረግም ቤተሰባዊ ኃላፊነታችንን እና ግዴታችንን በመወጣት የገንዘብ አቅም ፈጥረን ወደሥራ መግባት ግድ አለብን።
ውድ የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ አባላት ይህን ጨቅላ ቤተሰብ በእግሩ ካቆምን በኋላ ሁላችሁም ልብ ውስጥ የቅዱስ ያሬድን አገር ያቀኑ እውቀቶች ለመጠቀምና ጥልቅ የፍልስፍና ሀሳቦቹን ለማበልጸግ የሚያግዙ ሀሳቦች እንደሚኖሯችሁ እንጠብቃለን። በሂደት ሀሳባችሁን የምታንሸራሽሩበትን ዐውድ ፈጥረን በጥልቀት እንድምንወያይ እንጠብቃለን።