ኢትዮጵያ ያሬዳዊ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ስነውበት እና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት
1. እንደ ሀሳብ
ኢትዮጵያ አጅግ በጣም ጥንታዊት፣ ትውፊታዊትና ባህላዊት አገር ነች፡፡ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤትና ቀደምት ምድር፡፡ ቀደምትና ጥንታዊ ስልጣኔ የናኘባት አገር ከሆነች ታዲያ እንደምን አሁን የዓለም ጭራ ሆነች የሚለው ጥያቄ እጅግ የሚያብከነክን ጥያቄ ነው፡፡ ሁሉም በተለያየ አጋጣሚ ጥያቄውን እያነሳ ዘመናት ተቆጠሩ፤ እኛም ዛሬ ይህንንው እንጠይቃለን፡፡
እንደ ምክንያት ከሚነሱት በርካታ ነጥቦች ዋናው ኢትዮጵያ ለቀደምት ስልጣኔዋ መሰረት የሆኑ እሴቶቿን፣ እውቀቷን፣ ጥበቧን፣ ፍልስፍናዋንና የክዋኔ ጥበብ ንድፈ ሀሳቧን ዘንግታ ከምዕራባውያን የትምሕርት ሥርዓት ጋር ተያይዞ እንደደለል በደፈቃት አስተሳሰብ፣ የባህል ወረራ፣ መጤ እውቀት ራሷን እየገዘገዘች በጥበብና በእውቀት የበለጸገ ማንነቷን አክስታና እሴቷን አፈራርሳ ከመሠረትዋ በመነቀሏ ነው የሚለው ምክንያት ነው፡፡ እውን ታዲያ ከሌላው ለመቀበል የራስን መልቀቅ ግድ ነበረብን ወይ? እያልን ከጥያቄ ወደ ጥያቄ እንሸጋገራለን። እውቀት ሰጥቶ የመቀበል መርህ እንጂ የአንድ ወገን ስጦታ አይደለም። በቅልውጥ እና በምጽዋት እውቀትና እውነት አገር አይሰራም፤ ትውልድ አይቀረጽም፡፡
ትውልድ ዛሬም ድረስ የሚብሰለሰልበትን ይህን ጥያቄ ለመመለስ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳውን የጥበብ በኩር ቅዱስ ያሬድን ማንሳታችን ግድ ነው። ከቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ የምንቀዳቸውን ንድፈ ሀሳቦች እና አገር አቅኚ እውቀቶቻችንን በማበልጸግ ለዘመናት ከምንፍገመገምበት አዘቅት መውጣት ይገባናል፤ እንችላለንም።
የቅዱስ ያሬድ አገር አቅኚ የተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ፣ የጥበብ፣ የሥነ ምግባር፣ የሥነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ፍልስፍና፣ የሥነ ፈለክ፣ የባህልና እሴት አደረጃጀት አስተምህሮው እና ቀመር ከ6ኛው እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመን የዘለቀውን የኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመን ናኝቷል። ኢትዮጵያ ከቅዱስ ያሬድ የወርቃማው ዘመን ትሩፋት ለዛሬው ትውልድ የተረፈ ሥልጣኔና ዘመን የማያስርጀው እሴትና ባህል ገንብታለች። ዛሬ በአራቱም ማዕዘናት በቁጭትና በትኩረት ለፍለጋ ታጥቀን የተነሳንው በዚህ ልህቀት የረቀቀውን ማንነትና እውቀት ምን አፈረሰው? ማን ሰለበው? ብለን ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ልብና ጥበብ ለፍለጋ ከወጣ የ6ኛውን ክፍለ ዘመን የዋጀ ጥበብ፣ እውቀትና እውነታችንን እናገኘዋለን።
በዚህ መሠረት ይህን እውቀት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ያሬዳዊ ጥበብ፣ ስነ ውበት፣ ስነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት ተቋቋም።
1.1. ኢትዮጵያ ያሬዳዊ ጥበብ፣ ሥነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት
ድርጅቱ በቅዱስ ያሬድ አገር አቅኚ እውቀቶችና ሕይወቱ ዙሪያ ከሁለት አሠርታት ላላነስ ግዜ ሲብሰለሰሉ በኖሩ ኢትዮጵያውያን የተመሠረት ሲሆን ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ እነሆ ሁለት ዓመታት እያስቆጠረ ነው። ድርጅቱ ቅዱስ ያሬድን አብነት አድርጎ ሊሰራ ያሰባቸው በርካታ ተግባራት አሉ። ሀሳቡና ተግባሩ እውን ሆኖ የተለመው ትልም ግቡን የሚመታው የሁሉንም ተሳትፎ አስተባብሮ ሲሰራ መሆኑን ያምናል።
በዚህ መሠረት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ ሆኖ በጥቂቶች የታለመውን ሀሳብ የጋራ አድርገን የምንንቀሳቀስበትን ማዕቀፈ እሳቤ እውን ማድረግ ይገባናል። የቅዱስ ያሬድን አስተምህሮና ንድፈ ሀሳባዊ የእውቀት ፈለግ ተከትለን የተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ፣ ሥነ ውበት እና ክዋኔ ጥበብ ፍልስፍናችን ላይ ትኩረት ሰጥተን ከሰራን በስልጡን ስነ ልቡናዊ አደረጃጀት የመጠበብ አቅማችን ይጎለብታል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት አዘቅት ወጥታ በስልጣኔ ምህዋር እየተሸከረከረች የናፈቀችውን የከፍታዋን ዘመን ትቀዳጃለች፡፡ ወርቃማ ዘመንዋን ለመናኘት ከቅዱስ ያሬድ ፍልስፍና የሚቀዳ አገር በቀል እውቀቶቻችንን ከቀደምት የብራና ጽሑፎቻችን፣ ቅርሶቻችንና የወግ ቁሶቻችን ላይ እያየን መጻዒውን የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ ለማቅናት እንችላለን፡፡
- ዝርዝር አላማዎች
- የቅዱስ ያሬድን ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ስነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ንድፈ ሀሳብ መሠረት በማድረግ አገር በቀል እውቀቶችን ማበልጸግ እና የኢትዮጵያን ወርቃማ ዘመን ለማምጣት አስተዋጽዖ ማድረግ፤
- የቅዱስ ያሬድ የተፈጥሮና ማሕበራዊ ሳይንስ ንድፈ ሀሳቦች፣ የሥነ ምግባር፣ የክዋኔ ጥበብና የስነ ውበት ፍልስፍና እውቀቶችና ትምሕርቶች፤ ትምሕርትን የማስፋፋት ዘይቤው ከመደበኛ ሥርዓተ ትምሕርት ጋር ተጣጥሞ አገራዊ ፋይዳ እንዲኖረው ማድረግ፤
- ቅዱስ ያሬድ እንደ ኢትዮጵያዊ የእውቀትና የጥበብ አባት በዜማና ዜማ ድርሰቱ፤ ክዋኔ ጥበብና ስነ ውበት ፍልስፍናው ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማድረግ በአገር በቀል እውቀትነቱ ፋይዳ እንዲኖረው የጥናትና ምርምር ሥራዎችን መሥራት፤
- የቅዱስ ያሬድን አገር በቀል ንድፈ ሀሳባዊ እውቀቶችና ፍልስፍናዎች መሠረት ያደረጉ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያላቸውን የኪነ ጥበብ ስራዎች በሥፋት መስራት፣ ማህበራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው፣ ለገጽታ ግንባታና አገርን ለማስተዋወቅ ተገቢው ሚና እንዲኖረው ጥናታዊ ወርክሾፖች፣ ሲምፖዚየሞችና ትምሕርታዊ ሴሚናሮችን በማካሄድ ግንዛቤ መፍጠር፤
- የክዋኔ ጥበብና ስነ ውበት ፍልስፍናዎቹ ተቋማዊ እንዲሆኑ የጥበብ ማዕከላትን/ Creative Center ማቋቋም እና ቀደም ብለው ሲሰሩ የነበሩ ካሉ በአጋርነት መሥራት እና ማስፋፋት፤
- የክዋኔ ጥበብና ስነ ውበት ፍልስፍናዎች ተቋማዊ እንዲሆኑ ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትን ማቋቋም፣ በተመሳሳይ ከሚሰሩ የትምሕርት ተቋማት ጋር በአጋርነት ለመሥራት ስልት ይዘረጋል፤
- ከቅዱስ ያሬድ እውቀትና ጥበብ የተቀዱ አገር በቀል ንድፈ ሀሳቦችንና ፍልስፍናዎችን መሠረት በማድረግ በእውነተኛ ታሪኮች ላይ በተመሠረተ ፈጠራ የልጆች ተረት መጻሕፍት፣ የልጆች የድራማ መጻሕፍት፣ አጋዥ የትምሕርት መማሪያ እና ልዩ ልዩ ጥናታዊ መጻሕፍት በአገር ውስጥና በውጪ አገር የተለያዩ ቋንቋዎች እንዲጻፉ ደራሲያንን ማበረታታትና ማገዝ፣ ለሕትመት ማብቃትና እውቀቶቹና ፍልስፍናው በመላው ዐለም እንዲሰርጽ እና ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ አስተዋጽዖ ማድረግ፤
- ለአገልግሎት የተዘዋወረባቸው እና ለጽሑፍ የተጠቀመባቸው ቁሳቁሶች፣ የወግ ቁሶች የሚገኙበትን ስፍራዎች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመሥራት ቱሪዝምን ለማሥፋፋት አስተዋጽዖ ማድረግ፤
- የተለያዩ ባህላዊና የቤተክርስቲያን መገልገያ የወግ እና ትውፊታዊ ቁሶችን ማለትም መቋሚያ፣ ጽናጽል፣ ከበሮ፣ ደወል፣ ጻህል፣ ጽዋ፣ በትረ መስቀል፣ አልባሳትና የመሳሰሉትን በተጓዳኝ በማምረት ቁሶቹ እንዳይጠፉ ከማድረግ ባሻገር ነባሩ የሥራ ባህል እንዲዳብርና የፈጠራና ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲጎለብት ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ተቋማት እንዲመሠረቱ የቴክኒክ፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ወጣቶችን በማደራጀትና በማስፋፋት ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር፤
- የቅዱስ ያሬድ አገር በቀል ንድፈ ሀሳባዊ እውቀቶች፣ ትምሕርቶችና የትምሕርት ዘይቤ፣ የክዋኔ ጥበብና ስነ ውበት ፍልስፍናዎች እንዲስፋፋ የቅዱስ ያሬድ ጥበብ አድናቂዎች ቤተሰብ/ St.Yared Wisdom Family ይመሠርታል፤ ከሚመስሉት ጋር በአጋርነትም ይሰራል፡፡
- የቅዱስ ያሬድን አገር በቀል አስተምህሮ መሠረት አድርጎ የታሪክ፣ የስነ ምግባር፣ የአርትና የፍልስፍና ትምሕርቶች የሚሰጥባቸው የአንደኛና ሁለተኛ ትምሕርት ቤቶችና የጥናትና ምርምር ዩኒቨርስቲዎችን ከቀደምትና ነባር የአብነት ትምሕርት ቤቶች ጋር በማስተሳሰር ወይም ተስማሚ የሆነ አደረጃጀት ፈጥሮ በኢትዮጵያ ምድር ማቋቋም፤
- የአብነት ትምሕርት የሚሰጥባቸው ዋና ዋና ሥፍራዎች የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ፣ እንደ አገር በቀል እውቀትነቱና ጥበብነቱ በግዜ ሂደት እየተመናመነ እንዳይጠፋ እንደ ማንኛውም ሙያ ትውልዱ እንዲማረው ማበረታታትና ተገቢውን ክብርና ጥቅም እንዲያስገኝ መሥራት፤
- የወላጆቻቸውን እንክብካቤ ተለይተው ለአብነት ትምሕርት በተለያዩ ሥፍራዎች እውቀቱን ለመገብየት የተሰማሩ ታዳጊና ወጣት ተማሪዎች የመጠለያ፣ የምግብና የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ የበኩሉን አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡
- ከጥበቡ በተቀዳ አገር በቀል እውቀት እንደ አገር በስነ ምግባር ታንጸው ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጡ ወጣት ዜጎች በውስጣቸው ያለውን እምቅ ብቃት ተረድተው ለራሳቸውም ለሀገርም ጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ የማስተማሪያ መንገዶችን በመጠቀም ስለሰላም፣ ስለአገር አንድነት፣ ግጭት አፈታት ስልቶችን፣ ማሕበራዊ ሕይወትን በሚያደላድሉ እና ስነ ልቡናዊ አደረጃጀትን በሚያንጹ አገር በቀል ንድፈ ሀሳቦች ተመሥርቶ ማስተማርና ማነቃቃት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአጋርነት መሥራት፤
- በድርጅታችን ስር ለሚገኙ ድጋፍ ለሚያሻቸው አካላት ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ ማለትም ቁሳዊ፣ የገንዘብና ሙሉ ሰብዕና እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ስልጠናዎችንና አቅርቦቶችን እንዲያገኙ ማድረግ፣
- በጎዳና ዳር ለሚገኙ ህጻናትና ወጣቶች የአስተሳሰብ ለውጥ ስልጠናዎችን በመስጠትና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት በቅዱስ ያሬድ አገር በቀል እውቀትና ጥበብ ታንጸው ህይወታቸው እንዲቀየር መስራት፤
- የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችና ዘጋቢ ፊልሞች በማዘጋጀት እንደ አገር ያለንን ወጥና ያልተበረዘ ኢትዮጵያዊ ትውፊት፣ እሴትና ባህል በማስተዋወቅ ተንቀሳቃሽ ኦዲዮ ቪዥዋል ትርዒቶችን፣ የመድረክ ትርዒቶችን፣ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድራማዎችን፣ መልቲ ሚዲያ ትርዒቶችን ከፍ ባለ ሙያዊ ብቃት ኢትዮጵያዊ መልክ ይዘው በስፋት በማቅረብ ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽዖ ማድረግ፤
- ከአስተምህሮው የተቀዱ አገር በቀል እውቀቶችን በመተንተንና ጥናታዊ ምርምር ሥራዎችን በማቅረብ ግንዛቤ የሚፈጥሩ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ቶክ ሾው ፕሮግራሞችንና የአዳራሽ ውስጥ አነቃቂ ንግግሮች በማዘጋጀት በመላ አገሪቱና በውጪ አገር እየተዘዋወሩ የአገር በቀል እውቀቶቻችንንና ጥበብ አገራዊ ፋይዳ በማስተዋወቅ ለአገር ገጽታ ግንባታና የሕዝብ ግንኙነት ስራዎች አስተዋጽዖ ማድረግ፡፡
- ማስፈጸሚያ ስልት
- ደርዝ ያላቸው የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በመሥራት የቅዱስ ያሬድን አስተምህሮ ለማስፋፋት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሥራት።
- በየደረጃው ለተለያዩ ቡድኖችና የሙያ ዘርፍ ትምሕርታዊ ሴሚናሮችንና ወርክሾፖችን በማዘጋጀት ግንዛቤ መፍጠር፡፡
- ዓላማውን የሚቀበሉና በዚህ ላይ ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በቤተሰብነት እንዲታቀፉ ማድረግ፡፡
- የኤሌክትሮኒክስና ሕትመት መገናኛ ብዙኃን አውታሮችን በተገቢው ደረጃ መጠቀም፡፡
- አስተሳሰቡ በመላው ሕብረተሰብ እንዲሰርጽና ተቀባይነት እንዲያገኝ ከአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ የሚዘልቅ የአድናቂዎች ቡድን በመመሥረት ግንዛቤ መፍጠርና ማሳተፍ፤
- ከዓላማው ጋር ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችን እና ተቋማትን አጋር በማድረግ በሰፊው የሚሰራበትን ስልት ይፈጥራል፡፡
- የሚጠበቀው ውጤት
- ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ክብሯና ከፍታዋ ትመለሳለች፤ ወርቃማ ዘመንዋንም ትናኛለች፡፡
- ኢትዮጵያ በቀደመ ስልጣኔዋ በዐለማችን ከሚከበሩና ከሚፈሩ ታላላቅ አገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡
- ኢትዮጵያውያን የሚኮሩባትና በተደላደለ ማሕበራዊ ሕይወት የሚኖሩባት ታላቅ አገር ትሆናለች፡፡
- የሥራ ባህላችን ተቀይሮ፣ በአገር በቀል እወቀቶቻችን ማህበራዊ ችግሮቻችንን እየቀረፍን ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት የምናደረጅባትን ኢትዮጵያ እንፈጥራለን፡፡
- ምክንያታዊና ሚዛናዊ በሆነ የተረጋጋ ስነ ልቡና አደረጃጀት ራሳችንን ችለን በመቆም በእውቀትና በጥበብ የልጆቻችንን ኢትዮጵያ እንሰራለን፡፡