የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ አመሠራረት

ቤተሰብ ታላቅ ማህበራዊ ተቋም ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በትውፊትና ማሕበራዊ ሳይንስ ንድፈ ሐሳብ ትንተና ቤተሰብ የተቋማት ሁሉ እናት ተቋም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ብቻውን አይደለም፤ በቤተሰብ መልክና ቅርጽ ነው የተፈጠረው። አዳም ውስጥ ሔዋን ነበረች። አዳምና ሔዋን መሥርተው ልጆች ወልደው ዘር ተክተዋል። በቤተሰብ የጀመረው መዋቅር ስፍቶና አድጎ ነው ማህበረሰብ እና ሕዝብም አሕዛብም የሆነው። ዳግማዊ አዳም የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ለም ሲመጣ ይህንንው ነው ያደረገው። በቤተሰብ ውስጥ አድጎ የማዳን ሥራውንም ሲጀምር የተግባራቱ ሁሉ መጀመሪያ ያደረገው ቤተሰብ መመሥረት ነው፡፡

ሰዎችን ከየአካባቢው እየመረጠ የቤተሰብ አባላትን ማሰባሰብና ታላቅ ቤተሰብ ይፈጥር ነበር፡፡ በኋላ ደቀ መዝሙሩ የሆነውና ቅዱስ ወንጌሉን እስከመጻፍ የአገልግሎት ክብር የተሰጠው ማርቆስ እናት ቤት ተቀምጦ ቤተሰቡን ቤተሰብ አደረገ፡፡ በግዜ ሂደት ቀራጩን፣ ዓሣ አጥማጁን፣ ጸሐፊውንና በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሉትን በእሱ ሚዛን ምርጦች የሆኑትን አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርትን አሰባስቦ ሐዋርያትን በአንድ ቤተሰብ ጥላ ስር አዋላቸው፡፡ ከዚሁ ጋር ቤተሰቦቼ የሚላቸው አልዓዛርና እህቶቹ ማርያና ማርታ ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚያም ሰላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት፤ ሰባ ሁለቱን ላእካነ አርድዕት፣ አንድ መቶ ሃያ ቤተሰቦችና ሌሎችም በየደረጃው የተለያዩ ቤተሰቦችን መሠረተ፡፡ በሄደበት እየተጓዙ፣ ውሎ ባደረበት ውለው እያደሩ ትምሕርቱን የሚከታተሉ ቤተሰብም ሆኑ፡፡

ይህ ቤተሰብ በመከራውና እንግልቱ ሳይለይ ተከትሎታል። በኋላም እኒህን ቤተሰቦች ይዞ በእርሱ መሠረትነት ታላቋን ቤተ ክርስቲያን መመሥረት ቻለ፡፡ በምድራዊ ሕይወት ጉዞው ያልተለዩት እጅግ የቀረበ ቤተሰባዊ ግንኙነትና ተከታይነት ዕድል የገጠማቸው ደቀ መዛሙርትና ሌሎቹ ቤተሰብ አባላት ሁሉ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ይዘው በየስብከተ አገራቸው ተሰማርተው  ክርስቲያናዊ ሕይወትንና ወንጌልን አስተምረው ክርስትናን በማይነዋወጥ አለት ድንጋይ ላይ አጸኑ መንጋውንም ጠብቀው ከጌታቸውና ከመምህራቸው የተሰጣቸውን ቤተሰባዊ አደራ ተወጥተው ዛሬ ለደረስንበት አብቅተውናል፡፡

ይህ ታላቅ አብነት አለው። በዚህ ዘመን ቅዱስ ያሬድን ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ እውቀትና እውነት በማበልጸግ ለተነሳሳን እኛ የምንሻውን ተግባር ለመከወንና የታለሙትን ተቋማት ለማቆም የምንችለው አንድ ቤተሰብ ስንሆን ብቻ ነው። በቤተሰባዊነት የስሜት ቁርኝት ፈጥረን በልብ ጉርብትና እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ አፍ ተናጋሪ በነገር ሁሉ ጸንተን እንቆማለን። የምንመሠርተውም ይህ ታላቅ ቤተሰብ በዚህ የቤተሰብ አደረጃጀት መልክና ቅርጽ ይሆናል፡፡ ይህ አደረጃጀት ትውፊታዊውን ቤተሰብ መሠረት ከማድረግ ባሻገር ለአዲሱ ትውልድ የትርክት አብነትና ተምሳሌትም ይሆነዋል፡፡

ችግር በፈተና የማይፈታ፤ በምድራዊ ደስታ፣ ሀብት ጸጋ የማይነሆልል፤ በምድራውያን ሥልጣን የማይረታ፤ የቅዱስ ያሬድን አገር አቅኚ እውቀቶች በማበልጸግ ቤተሰቡ የሚያበረክተው ጥቅም ቋንቋ ሊገልጸው አይቻለውም፡፡ ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት ፈተናና ከሚገዳደራት ኋላ ቀር (የተኮረጅ፤ ኢትዮጵያን የማይመስል ምዕራባውያን ውድቅ እሳቤዎችና የፈረሱ እሴቶቻቸው) አስተሳሰብና አስተምህሮ ይታደጋታል፡፡ በጠንካራ ቤተሰባዊ አንድነት ጸንተን ስንገኝ አነሳሳችን የሰመረ፤ አካሄዳችን የቀና ሆኖ ያለምነውን ግብ እናሳካለን፡፡

በዚህ መሠረት ቅዱስ ያሬድን ምክንያት አድርገን የተሰባሰብን እኛ በቅዱስ ያሬድ ስም እንደ ቤተሰብ ቆመን በአንድ መቶ ሃያ ቤተሰብ የበኩር ልጆች ሕብረት የካቲት 21 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት ከእንግዲህ  የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ ሆነን በአንድ ቆመናል፡፡

ከእንግዲህ በኋላ ይህ ቤተሰብ በኩር አባል ሁሉ በ1ኛ መጽሐፍ ስማችን ሰፍሮ የቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያው ትውልድ ሆነን የራሳችንን ታሪክ በደማቁ መጻፍ ጀምረናል፡፡ ይህን ቀና መንገድ ተከትለው የመጀመሪያው የቅዱስ ያሬድ ትውልድ ለመሆን በመንፈሳዊ ቅናት ለሚነሳሱ ወንድሞቻችን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተገቢውን ግዴታቸውን እየተወጡ እስከ ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓመተ ምሕረት ድረስ በመመዝገብ የመጀመሪያው የቅዱስ ያሬድ ትውልድ በመሆን ይህን ቤተሰብ መቀላቀል ይችላሉ፡፡

በዚህ ሂደት የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ 1ኛ ትውልድ 1ኛ መጽሐፍ፣ 2ኛ መጽሐፍ፣ 3ኛ መጽሐፍ፣…እያለ እስከ ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓመተ ምሕረት ድረስ የተመዘገቡ የመጀመሪያው ትውልድ ዘመን ቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡

ይህ ቀን ከዚያ በኋላ 2ኛ ትውልድ፣ 3ኛ ትውልድ እያለ መላውን ኢትዮጵያውንና የሰው ዘር የቅዱስ ያሬድ ቤተሰብ ለማድረግ የመሠረት ድንጋይ የጣልንበት ታሪካዊ ቀን እነሆ ዛሬ ይፋ ሆነ፡፡

ይህ ቤተሰብ ከማንኛውም ፖለቲካ አስተሳሰብ የጸዳ፣ ለሰው ክብር ከማይመጥኑ የዘር ወይም የብሔር፣የቋንቋ ውርክቦች ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌለው፣ ከኑፋቄና ከኃይማኖት ህጸጽ ራሱን የሚከላከል በመንፈሳዊ ስብዕናቸው የተረጋጉ አባላት የተሰባሰቡበት የቅዱስ ያሬድን ጥበብ፣ እውቀትና እውነት ከማበልጸግ ውጪ ለማንኛውም ግብር የማይተባበር ቤተሰብ ነው፡፡