የቅዱስ ያሬድ ትውልድ፣ እድገትና ትምሕርት

admin
Document
09 Mar, 2023

ስለቅዱስ ያሬድ የሚያወሱ በርካታ መጻሕፍትና ጥናታዊ መጣጥፎች አሉ፡፡ በርካታዎቹ ከውልደት በአካለ ስጋ ተለየ እስከሚባልበት ግዜ ድረስ ያለውን ሂደት ስለቅዱሱ የሚያወሩትን ጥንታዊውን ድርሳን፣ ገድልና ስንክሳር መሠረት አድርገው ሲጽፉ ጥቂት ምንባባት ግን ውልደቱን በተመለከተ የተለየ ወቅት ሲጠቅሱ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ቅዱስ ያሬድ ነበረበት ከሚባለው ዘመን እና የነገስታት ታሪክ ጋር የተጠቀሱት ማህበራዊ እውነታዎች የማይጣጣሙና በእጅጉ የተፋለሱ ሆነው በመገኘታቸው የቅዱስ ያሬድን ድርሳን፣ ገድልና ስንክሳር መሠረት ማድረግ ግድ ይላል፡፡     

ቅዱስ ያሬድ በእናትና አባቱ በኩል እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ቤተሰቦች የዘር ሐረጉ ይመዘዛል፡፡ የትውልድ ስፍራው መደባይ ታምሪ በሚባል አካባቢ ሲሆን ሚያዝያ 5 ቀን በ505 ዓ.ም በዘመነ ማቴዎስ ከአባቱ አብዩድ (ይስሐቅ) እና ከእናቱ ታውክልያ (ክርስቲና) በአክሱም አቅራቢያ በምትገኝ መንደር ውስጥ ተወለደ፡፡ ቅዱስ ያሬድ አባቱ አብዩድ በሕጻንነቱ ሞተ፡፡ ከዚህ በኋላ እናቱ ታውክልያ ልጇን በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንቶ በበጎ ምግባር ተወስኖ እንዲኖር በሀይማኖት ኮትኩታ አሳደገችው፡፡

እንደ ሊቀ ማዕምራን አባይ አጥሌ አገላለጽ የቅዱስ ያሬድ የዘር ሐረግ ለጥበብ ልዩ ዋጋ በመስጠት ኢየሩሳሌም ድረስ ከሄደችው ንግስተ አዜብ ማክዳ ትውልድ ይመዘዛል፡፡ ይህም በአባቱ በኩል ከኩሽ ዘር ከተወለደው በምድረ መደባይ ዘንዶውን ገድሎ ለመንገስ ከበቃው አጋቦን አጋቦስ ጀምሮ ይቆጠራል፡፡

“… አጋቦስ ኩርፎን ወለደ፣ ኩርፎ ሰርፎን ወለደ፣ ሰርፎ አቂላን ወለደ፣ አቂላ ጵርስቅላን ወለደ፣ ጵርስቅላ ዝዮን ወለደ፣ ዝዮ መዝዮን ወለደ፣ መዝዮ ዳግማዊ አጋቦስን ወለደ፣…” ቅዱስ ያሬድ በዓለም መድረክ ገጽ 19

ቅዱስ ያሬድ አባቱን በሕጻንነቱ በማጣቱ ሰባት ዓመት ሲሆነው እናቱ ታውክልያ የአክሱም ቄሰ ገበዝ ለነበረው ወንድሟ መምሕር ጌዴዎን የቤተ ክርስቲያን ትምሕርት እንዲያስተምርላት ሰጠችው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ከአጎቱ መምህር ጌዴዎን ዘንድ ፊደል መማር ጀመረ፡፡ መምህሩም በቅርብ እየተከታተለ ከጓደኞቹ ሕጻናት ጋር ፊደለ ሐዋርያትን፣ አራቱን ወንጌላትና መልእክታትን ከጨረሰ በኋላ ዳዊት መማር ጀመረ፡፡

ይሁን እንጂ ዳዊት መማር የጀመረው ሕጻን የዳዊት መዝሙርን ከጓደኞቹ እኩል መያዝ አስቸገረው፡፡ አጎቱ ከጓደኞቹ እኩል በርትቶ ቀለም እንዲይዝ ቢከታተለውም በአግባቡ መያዝ ቢያስቸግረው ጓደኞቹም እንዳፌዙበትና መመህሩም እንደገረፈው በታሪኩ ይጠቀሳል፡፡ በዚህ የተማረረው ቅዱስ ያሬድ ከአጎቱ ተደብቆ ወደእናቱ አገር ወደ መደባይ ወለል ጠፍቶ ሄደ፡፡

በመንገዱ ላይ የምትገኝ ማይኪራህ በምትባል ቦታ ውኃውን ከወራጅ ወንዝ ተጎንጭቶ ከአንዲት ዛፍ ጥላ ስር እንደ ተቀመጠ በአጋጣሚ ዛፉን ለመውጣት የምትውተረተር ትል አየ፡፡ ትሏ ለስድስት ግዜ ያህል ስትወድቅ ስትነሳ ከቆየች በኋላ በሰባተኛው ከዛፉ አናት ወጥታ ከዛፉ ፍሬ ስትመጥ ያያል፡፡

በዚህ ሁኔታ የራሱን የትምሕርት ክብደትና መውደቅ መነሳት ምስጢር እያሰላሰለ የመንፈስ ብርታት የተሰማው ሕጻን ትሏ ይህን ማድረግ ከቻለች እኔማ ከእሷ የምበረታው ሰው እንደምን አቃተኝ ብዬ በሽንፈት ከቀለም ገበታ እለያለሁ በሚል ቁጭት ወደመምህሩ ተመልሶ አጎቱን መምህር ጌዴዎንን ይቅርታ ጠይቆ ትምሕርቱን በትጋት መማር ቀጠለ፡፡ ከዚህ በኋላ በአጭር ግዜ ውስጥ መቶ ሀምሳውን የዳዊት መዝሙር፣ መኃልየ ነቢያትንና መኃልየ ሰሎሞንን፣ውዳሴ ማርያምን፣ ሰማንያ አንዱን መጻሕፍት ንባቡን ከነትርጓሜው መማር ቻለ፡፡ ቅዱስ ያሬድ በተማረበት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን የዲቁና ማዕረግ ስልጣነ ክህነት ተቀብሎ ከማገልገሉም ባሻገር አጎቱ በሞተ ወቅት በአጎቱ እግር ተተክቶ የብሉይና ሐዲስ መምሕር ሆኖ ንባብና ትርጓሜ መጻሕፍትን በማስተማር በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል፡፡

ከዚያ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ምድራዊ ጥበብ እና ሰማያዊ ጥበብ ተገልጾለት አምስቱን ጸዋትወ ዜማ ድርሰቶች ደርሷል፡፡ በሥራዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት በመጠቀም የክዋኔ ጥበብን በስነ ውበት ናኝታ ዐለምን በሚያስደምሙ መንፈሳዊ ዝማሬዎቿና አገልግሎት አፈጻጸም ሥርዓቷ ገናና ስምና ክብር አግኝታለች፡፡

በዚህ የጠነቀቀ ስልት ቅዱስ ያሬድ በተነሳበት በዚህ ወቅት የክርስትና እምነት እጅግ የተስፋፋበትና ቤተ ክርስቲያናት የቀደመ የግንባታ ጥበባቸውን አልቀው በሰሩት አዲስ ቅርጽ በስፋት የታነጹበት ነበር፡፡ የቅዱስ ያሬድ ደቀ መዛሙርት ራሳቸውን ችለው ወንበር ዘርግተው በተለያዩ ጉባኤ ቤቶች ዕውቀቱን በማስፋፋት የቤተ ክርስቲያን ትምሕርት ቤቶችም ተበራክተዋል፡፡ በርካታ ገዳማትም ተገድመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሰው አስተሳሰብና ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ፍጹም የተረጋጋና የሰከነ ስነ ምግባራዊነት፣ ግብረ ገባዊነት፣ ምክንያታዊነት እና መንፈሳዊነት የናኙበት በመሆኑ 6ኛው እስከ 9ኛው ክፍለ ዘመን ለኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ወርቃማ ዘመንዋ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ (ኦርቶ.ተዋ...ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስ.2000 . ገጽ 18)

በአንድ ወቅት ቅዱስ ያሬድ በተመስጦ ውስጥ ሆኖ ዜማውን በመዘመም ላይ ሳለ በቅዱስ ያሬድ ዜማ ፍጹም ተመስጦ ውስጥ የሚገቡት አጼ ገብረ መስቀል ዐይን ዐይኑን እተመለከቱ እንደእርሱ ሲዘምሙ በወርቅ ዘንጋቸው የቅዱስ ያሬድን እግር ወግተውት ብዙ ደም ፈሰሰው፡፡ አጼውም እጅግ ደንግጠውና አዝነውበጣም ጎድቼኃለሁና ምን ልካስህበሚል እስከ መንግስታቸው እኩሌታ የፈለገውን ሁሉ ሊያደርጉለትና ሊሰጡት ቃል ይገቡለታል፡፡ ቅዱስ ያሬድም ልቡና መንፈሱ ፍጹም ከምድራዊ ፍላጎት ጋር አልነበረምና በእግዚአብሔር ጸጋ በአክሱም ከተማ ብዙ መቆየቱንና በእግሩም ተተኪ ብዙ ደቀ መዛሙርትን ማፍራቱን ገልጾለት የቀረው ዕድሜ ዘመኑን በጸሎትና በብህትውና ማሳለፍ እንደሚፈልግ በምናኔ እንዲኖር ያሰናብተው ዘንድ ለመነው፡፡

አጼ ገብረ መስቀል ያልጠበቀውና እጅግ አስደንጋጭ ጥያቄ ሆነበት፡፡ እንኳንስ ጣዕመ ዜማውን ሰምቶ ይቅርና መልኩን በማየት የሚሰማውን ሀሴት ማጣቱ ሲታሰበው ጭንቅ ቢሆንበትም ቃሉን ማጠፍ አልተቻለውምና ተላቅሰው ተሰነባበቱ፡፡ መላው የአክሱም ካህናትና ምዕመን በከፍተኛ ሀዘን ተውጠው ጉዞውን ወደ ደቡብ አቅጣጫ አቅንቶ ወደ ሰሜን ተራራዎች ተጓዘ፡፡ ካህናቱና ሕዝቡም እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ በልቅሶ ሸኙት፡፡ ተከዜ ወንዝ ላይ ሲለያዩ በዜማ ስንብት አድርጎላቸዋል፡፡ሰላመ ነሣእነ ወሰላመ ኃደግነ ለክሙ ወሰላመ እግዚአብሔር ምስለ ኩልክሙ፤ ወሰላመ እግዚአብሔር እንተ ኩሉ ባቲ ተሀሉ ወትረ ምስለ ኩልክሙትርጓሜውም ሰላምን ተቀበልን፤ ለእናንተም ሰላምን ተውንላችሁ፤ የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ ሁሉም የሚገኝባት የእግዚአብሔር ሰላም ሁልግዜ ከእናንተ ጋር ትሁን ማለት ነው፡፡ ጾመ ድጓ ቅዱስ ያሬድ ከዘወረደ ሐሙስና ከምኩራብ ሐሙስ

በዚህ ጣዕመ ዜማ ተሰነባብተው የተከዜን ወንዝ ተሻገረ፡፡ የወንዙ ፏፏቴና ጎርፍ እንደአንበሳ ሲጮህ በሰማ ግዜአኅለፍኮሙ በእግር እንተ የብስ ማዕከለ ባህረ ተከዜበተከዜ ባህር መካከል በእግር እንደሚሻገር በደረቅ አሻገርካቸው…”እያለ በረቀቀ የዜማ ድርሰት ምስጢር እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲሄድ አንዲት ሴት ሰምታወይ ቃል እንዴት አንጀት ይበላል ምንኛስ ያሳዝናል እያለች ደጋግማ በማድነቅ ስትናገር በመደመጧ ያች ቦታ እስከ ዛሬወይ ቃልበመባል ትታወቃለች፡፡ በጎንደር ክፍለ ሀገር በደባርቅ አካባቢ ወይ ቃል ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ትባላለች፡፡   

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ ሰሜን ተራሮች በማቅናት ጸለምት ወጥቶ ብርድ በጸናበት እና በረዶ በተከማቸበት ሳኔር ተብሎ በሚጠራ በሐዊ ዐምባ ጽሙና ዞን ተቀመጠ፡፡ በዚያም በብዙ ትጋት በጾምና በጸሎት ተወስኖ ስብሐተ እግዚአብሔር እያደረሰ ጉባኤ ዘርግቶ፣ ትምሕርት አስፋፍቶ ከሱራፌል መላእክት እንደተማረው አድርጎ ከጸለምት፣ ከሰሜን፣ ከአገውና ከሌላ አገር ወደ እርሱ የሚመጡትን ሰዎች ሁሉ ማሕሌተ እግዚአብሔር እያስተማረ ኖሯል፡፡ ይህ ቦታ አሁን ድረስ በስሙ ደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ ገዳም በሚል ስያሜ በመጠራት ይታወቃል፡፡

Tags