የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች

admin
የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች
27 Feb, 2024

አምስቱ ጸዋትወ ዜማ በመባል የሚታወቁት የቅዱስ ያሬድ ስራዎች ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬና መዋስዕት ናቸው፡፡ እነዚህም በሰከንድ፣ በደቂቃ፣ በሰዓት፣ በቀን፣ በወራትና ዓመት ቀመር የግዜ ወሰን ተበጅቶላቸው ከዓመት ዓመት የሚደረሱ ጣዕመ ዜማዎችና ምንባባት ሲሆኑ ድርሰቶቹ ግጥማዊ ምት ያላቸው/Poetic፤ የትውን ጥበብ አላባውያን ጎልተው የሚስተዋልባቸው ክዋኔ ጥበባት ናቸው፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰትና የዜማ ስራዎች በእነዚህ አምስት ክፍሎች ይከፋፈሉ እንጂ ቅዱስ ያሬድ በትርጉምና ትንተና ዘይቤው የግዕዝ ቅኔና የቅኔን ቅርጽ የፈጠረ ነው፡፡ በሂደት ከግዕዝ ቅኔ ስልት የአማርኛ ቅኔንም አስገኝቷል፡፡ ከዚህም ሌላ የራሱን ቅዳሴ ድርሰትና ዜማ ከመድረሱ ባሻገር በሌሎች ሊቃውንት የተደረሱ አስራ አራት ቅዳሴያትን የዜማ ድርሰቶች፣ በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የተደረሰውን ውዳሴ ማርያም ዜማ እንደሰራላቸው ይነገራል። ይልቁንም ለዜማ ማቅኛና ማጎልበቻ ሀሳቦችን በመጨመር ውዳሴ ማርያምን ተከታታይ የሆን /Episodic ቅርጽ በመፍጠር ለጸሎትና አገልግሎት ምቹ አድርጎታል።

በማህሌት የሚዘመሙ አቋቋም ዜማና መዝሙር ድርሰቶችን ጨምሮ አምስቱ ጸዋትወ ዜማ የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች የሚከተሉት ናቸው። እነዚህም-

      1.1. ድጓ

ድጓ የቅዱስ ያሬድ ትልቁ የድርሰት ዜማ መጽሐፍ ነው፡፡ ሊቃውንት ከምስጢሩ ፍቺ ተነስተው ከፊሎቹ ደግሞ ከቃሉ ፍቺ ተነስተው የተለያየ ትርጉም ይሰጡታል፡፡ ድጓ ማለት ድግድገ ድግዱገ ጽሕፈት ማለት ነው ይላሉ፤ ይህም ጽሑፉ የቀጠነ ማለት ሲሆን ደቃቅ ወይም ረቂቅ  ወይም ዜማ ቁዘማ ግጥም ማለት ነው፡፡ ሌሎችም ድጓ የሚለውን አላልቶ በማንበብ መቀነት የሚለውን ስያሜ በመስጠት ይህ ታላቅ የዜማ ድርሰት ለቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያ መቀነቷ ሆነ በማለት ይተረጉሙታል፡፡ የቃሉ ትርጉም እጅግ በርካታ ሲሆን ፍቺውና ምስጢሩንም በዚሁ ልክ ያራቅቁታል

የድርሰት ሀሳቦቹ ሙሉውን የቅዱስ ያሬድ ፍልስፍና የያዘ ሲሆን የስነ ፍጥረታትን ድንቅ አፈጣጠር እየፈተተ የመለኮትን ልዕለ ባህርይ ግጥማዊ በሆነ መልክ በዜማ ያወደሰበት ነው፡፡ ይኸውም የዓመቱን ቀናት በአራት ዐቢይ ክፍሎች ከፍሎታል፡፡ እንደ ሊቃውንቱ ማብራሪያ ድርሰቱን በአራት የከፈለበት ምክንያት አራቱ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በብሉይ፡- ዘመነ አበው፣ ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ መንግስት፣ ዘመነ ካህናት ሲሆኑ በሀዲስ ኪዳን ደግሞ ዘመነ ሐዋርያት፣ ዘመነ ሰማዕት፣ ዘመነ ሊቃውንትና ዘመነ መነኮሳትን ለማመልከት ነው ብለው ፈተውታል፡፡

            1.1.1.  ዮሐንስ

ይህ ክፍል ከመስከረም 1 እስከ ኅዳር 30 ቀን ድረስ ያለው ሲሆን በዜማው ከባድነትና በቁጥሩ ብዛት ከሌሎች ክፍሎች እጅግ የበለጠ ነው፡፡

​​​​​​​            1.1.2. ​​​​​​​​​​​​​​አስተምሕሮ

ከታኅሳስ 1 ቀን እስከ ፋሲካ ድረስ ባለው ግዜ የሚዘመር ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር መሐሪነትና ርኅራሔ በማውሳት ስለሚጀምር አስተምህሮ የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡

​​​​​​​​​​​​​​            1.1.3. ጾመ ድጓ

ይህ ከአስተምህሮ የድጓ ክፍል ሆኖ በጾመ አርባ ወቅት በነግህ፣ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንዲሁም ቅዳሜና በሌሊት ይዘመራል፡፡ የክርስቶስን መምጣቱንና ሰውን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት መውረዱንና ሰውን ለማዳን ሰው የሆነበትን ጥበብ እያራቀቀ ይተነትናል፡፡ የጾምን፣ የንስሐን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና የፍቅርን ጠቃሚነት አጉልቶ ያስተምራል፡፡

​​​​​​​​​​​​​​            1.1.4. ፋሲካ

         ከፋሲካ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን መጨረሻ ድረስ የሚደርስ የድጓ ክፍል ነው፡፡  

 

​​​​​​​      1.2.ምዕራፍ

ለቅዱስ ያሬድ ሁለተኛው የድርሰት መጽሐፉ ሲሆን ምዕራፍ የተባለበት ምክንያት በየመዝሙራቱ መሀከል ሃሌታና ድጓ እያስገባ ለመዝሙሩ ማረፊያ ስላበጀለት ነው፡፡ በዚህ ሰበብ ማረፊያ፣ መስፈሪያ፣ መኖሪያ ቦታ ሰፈር ተብሏል፡፡ (ኢሳ 11 -10) “ወይትዌከሉ ቦቱ አህዛብ ወይከውኑ ምዕራፈ ዘዚአሁ ክብር፤ ትርጓሜውም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይ ሥር አህዛብ ይፈልጉታል፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል፡፡በማለት የምዕራፍን ትርጉም ከነቢያትና ከዳዊት መዝሙር እያጣቀሰ ያብራራል፡፡ ይህ ከአምስቱ ጸዋጽወ ዜማ አንዱ የሆነው የቅዱስ ያሬድ ድርሰት መጽሐፍ በሁለት ዐበይት ክፍሎች የሚከፈል ሲሆን የዘወትር ምዕራፍ እና የጾም ምዕራፍ ይባላሉ፡፡

በዓመቱ ውስጥ ባሉት ቀናት፣ ሳምንታትና በኣላት ሁልግዜ በአገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን የጾም ምዕራፍ ለጾመ አርባ ብቻ አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ድርሰቱን ያቀነባበረው ከዳዊት መዝሙር፣ ከራሱ ድጓና ጾመ ድጓ ነው፡፡ ምዕራፍን ለመማር 150 የዳዊትን መዝሙራት፣ 15 የነቢያት ምዕራፎችንና 5 የመኃልየ መኃልይ ሰሎሞንን በቃል ሸምድዶ መያዝ ግድ ይጠይቃል፡፡ 

​​​​​​​​​​​​​​      1.3.ዝማሬ

የቃሉ ትርጉም ዘመረ አመሰገነ ካለው ግስ ይወጣል፡፡ ይህ የዜማ መጽሐፍ ከቅዳሴ ጋራ የተቆራኘ አገልግሎት ያለው ነው፡፡ስርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ የቁርባን ምሥጢር ለምዕመናን በሚሰጥበት ጊዜ ይዘመራል፡፡

​​​​​​​​​​​​​​      1.4.መዋሥዕት

የቃሉ ትርጉም አውሥአ መለሰ ካለው የግዕዝ ቃል ይወጣል፡፡ ቀጥተኛ ትርጉሙ መመላለሻ ወይም ምልልስ ማለት ነው፡፡ግራና ቀኝ በቅብብሎሽ እየተመላለሰ ስለሚባል ይህን ስያሜ ማግኘቱን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ በሌላ ትርጉሙ ደግሞ ሰዋስወ ነፍስ፤ የነፍስ መሸጋገሪያ እንደሚባል ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡

መዋሥዕት እንደ ሌሎቹ የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ሁሉ ከጸሎትነቱ ባሻገር ብዙ ምስጢራትን ያመሰጥራል፡፡ ነገረ ድህነትን፣ ነገረ ማርያምን፣ ነገረ ቅዱሳን እና ነገረ ሰማዕታትን ያመሰጥራል፡፡ በዚህ ድርሰት ውስጥ መዋሥዕት ዘልደት፣ ዘአስተርእዮ፣ ዘስቅለት፣ ዘቤተ ክርስቲያን፣ ዘማርያም፣ ዘጻድቃን፣ ሰማዕት የሚባሉ ክፍሎች አሉት፡፡ እሊህ ሁሉ በክዋኔ ጥበብ ተቀምረው በዝማሬ የሚደርሱ ሲሆን ስነጥበባዊ ዋጋቸውና የፍልስፍና መሠረታቸው እጅግ ጥልቅ ነው፡፡

​​​​​​​​​​​​​​      1.5.ቅዳሴ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጥቅም ላይ የዋሉ አስራ አራቱ ቅዳሴያት አሉ፡፡ የቅዳሴው ድርሰት ባለቤትነት የተለያዩ ሊቃውንት ቢሆኑም ቅዱስ ያሬድ ሥርዓተ ቅዳሴውን ጨምሮ የአስራ አራቱንም ቅዳሴያት ዜማውን ሰርቶላቸዋል፡፡ ይህም በመሆኑ በድርሰቱ የተካተቱት ሀሳቦች ዘመን ተሻግረው ለከዋኙም ሆነ ለተደራሲው ሳይሰለችና ሳይደበዝዝ ዝንተ ዐለም አዲስ ሆኖ እስከዛሬ የዘለቀና ዝንተ ዐለም ሊደበዝዝ በማይችል ጥራትና ጥልቀት እየተገለጠ ሕይወትንና ዐለምን የሚያስቃኝ ጥበብና ረቂቅ ስነ ውበት ነው፡፡

የቅዳሴውን ዜማ በሚሰራበት ሂደት ውስጥ ቅዱስ ያሬድ ድርሰቱን ለዜማ እንዲመች አድርጎታል፡፡ በዚህም የበለጠ ሥነ ውበት እንዲላበስና ምስጠሩም ለጆሮ በሚስማማ ስልት እንዲገለጥ አድርጓል፡፡ በዚህ መሠረት አንድም ለዜማ ማቅኛ እንዲሆን፤ አንድም ምስጢሩን ለምዕመናን ተደራሽ ለማድረግ የተጠቀመበት ስልት ነው፡፡